በወላይታና አከባቢዉ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ
በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር የተሰጠ መግለጫ
June 25, 2020
የወላይታና አጠቃላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ መዋቅራዊና ስልታዊ (systemic) በሆነ መንገድ በሚፈጸምበት መንግሥታዊ ጭቆናና
አፈና ለዘመናት ጎብጦ የኖረ ሕዝብ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ከዚሁ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ በደል ለመላቀቅ ላለፉት በርካታ
ዓመታት የፍትሕና የመሠረታዊ መብት ጥያቄ በማቅረብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገል መቆየቱም ይታወሳል። ከሕዝቡ የትግል
አቅጣጫዎች አንዱ ክልል በመሆን ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግሥታዊ መብት ማግኘት በመሆኑ ከቀበሌ አደረጃጀት አንስቶ እስከ ዞን
አስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ ሕዝቡ ተወያይቶ በአንድ ድምጽ ለሚመለከተው የመንግሥት መዋቅሮች ሁሉ በማስታወቅ ፍትሓዊና ሕጋዊ መፍትሔ
ሲጠባበቅ ቆይቶአል። በተለይም አንጻራዊ የለውጥ ብርሃን በፈነጠቀበት በዚህ ጊዜ ጉዳዩ በመንግሥት በትኩረት ታይቶ ወቅታዊና ተገቢው ምላሽ
ይሰጣል ተብሎ መጠበቁ ተገቢ ነበር።
ሕዝቡ ያቀረበውን ሕገ-መንግሥታዊና መሠረታዊ የመብት ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኮማንድ ፖስት በማፈን፣ በኮሚቴ
እየታየላችሁ ነው፣ ሳይንሳዊ ጥናት እየተደረገበት ነው በማለት፣ እንዲሁም በሠላም አምባሳደሮች ይጠናል በሚሉ የጊዜ መግዣ በሚመስሉ
ማንከባለያዎች በመጠቀም የሕዝቡ የመብት ጥያቄ ተገቢ መልስ ሳይሰጠው ሲጓተት ቆይቶአል። በአሁኑ ጊዜ ይኼው ሁኔታ ግለቱንና ጡዘቱን
ጨምሮ የወላይታን ሕዝብ እርስ በራሱ ወደማተራመስና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ወደማጋጨት ደረጃ እየደረሰ መሆኑ ይስተዋላል። በመሆኑም
ይህ ሁኔታ በእጅጉ ያሳሰበው በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር ከመላው ዓለም የአካባቢውን ተወላጆች ሐሳባቸውንና
ስሜታቸውን እንዲገልጡ ባለፉት ሳምንታት መድረኮችን በማዘጋጀት በስፋት ውይይት ተደርጎበታል። በነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ
የተንጸባረቁ ሓሳቦችን መነሻ በማድረግ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የአቋም መግለጫዎች አውጥቶናል።
- የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የወላይታ ሕዝብ በአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የራሱን ድርሻ በሚገባ ማበርከት እንዲችል፣ የኢኮኖሚ
ልማትም ፍትሓዊ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል፣ ባሕልና ቋንቋውን ማሳደግ እንዲችል፣ ባልተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር አገልግሎት
ማግኘት እንዲችል እና በአገሪቱ መንግሥትና ሕግ እኩል መታየት እንዲችል ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን ዕድል በመጠቀም ራሱን በራሱ
ለማስተዳደር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይና ወቅታዊ ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን። - የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የወላይታን ሕዝብ ሠላማዊና ሕጋዊ ጥያቄ ትርጉሙን ለማዛባት በለውጡ ማግስት እያመጹ ከሚገኙ ከተለያዩ
አካላት ጋር በማያያዝ የወላይታን ሕዝብ ስም የማጉደፍ፣ የጥያቄውን ተገቢነት ለማደብዘዝ፣ ብሎም የህዝብን ትዕግስት እንዲሟጠጥና
የአካባቢውን ሰላም በማናጋት ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ተብሎ የሚሰራው አደገኛ ሸፍጥና ሴራ በአስቸካይ
እንዲታረምና ህጋዊ የሆነው በክልል የመደራጀት ጥያቄ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት እንዲመለስ እንጠይቃለን:: - የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የወላይታ ሀዝብ ጥያቄ በማያሻማ ቃላት የተገለጸ ራስን በራስ ማስተዳደር እንጂ የማዕከልና የክላስተር ጥያቄ አለመሆኑን
ሕዝቡና ተወካዮቹ በተደጋጋሚ ገልጸዋል እየገለጹም ነው። ይህ እውነታ በግልፅ እየታወቀ በተቀናጀ መንገድ ከአጎራባች ወንድም ህዘቦች ጋር አላሰፈላጊ የሆነ
ግጭት ለመፍጠር በህዝባችን ላይ እየተካሄደ ያለው የተደራጀ ሴራና ስም የማጥፋት ዘመቻና ዕኩይ ድርጊት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ
በማስገባት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በአፋጣኝ እንዲያስቆም እናሳስባለን። - መላው የወላይታ ሕዝብ በበኩሉ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግሰታዊው ራስን በራስ የማሰተዳድር ጥያቄ የህልውናው ጥያቄ በመሆኑ በአንድነት መንፈስ
እስከፍጻሜው በሠላማዊ ና ሕጋዊ መንገድ ብቻ በፅናት እንድትታገሉ በአክብሮት እንጠይቃለን:: በዚህ ሰላማዊ ትግል እንደ ሲቪክ የዲያስፖራ ማኅበር
ከጎናችሁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ እናረጋግጣለን፡፡ - በተለያየ የዓለም ሃገራት የምትኖሩ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች በወላየታ ህዝብ ላይ እና በአጠቃላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን
የአስተዳደር በደልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በምትኖሩባቸው ሃገራት ላሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ለተለያዩ ተቋማትና ሕዝቦች፣ ዓለም አቀፍ
የሰብዐዊ መብት ድርጀቶችና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በማሳወቅ በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ ጫና ለማሳደር
የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ እያሳሰብን ያስተማራችሁን ማህበረሰብና የጋራ ሀገራችን ኢትዮጵያንም የምትረዱበት ወሳኝ ወቅት ላይ በመሆናችሁ በተለያዩ
ሚዲያዎችም ጭምር የሕዝቡን ድምፅ እእንድታጎሉ በአክብሮት እንጠይቃለን። - የወላይታ ዞን ምክር ቤትና የሕዝቡ ተወካዮች ምንም እንኳን የዘገየ ቢሆንም የክልልሉን ምክር ቤት ባለመሳተፍ ካሳያችሁት ቁርጠኝነት ጀምሮ ባወጣችሁትም
የአቋም መግለጫ ያለንን አድናቆት እየገለጽን አሁንም የሕዝብ አገልጋይነታችሁንና ወገንተኝነታችሁን በጽናት እስከመጨረሻው እንድትቀጥሉ እያሳሰብን
የወላይታን ዲያስፖራ እያስተባበረ የሚገኘው ማኅበራችን ከጎናችሁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ያስታውቃል። - በመጨረሻም የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በዚሁ ጉዳይ የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ለማበርከት መስዋዕት በመክፈል ላይ ለምትገኙ
በመንግሥት ኃላፊነት የምትገኙ የሕዝቡ ተወካዮች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት መሪዎች፣ የላጋዎች፣ ስላሳያችሁት
ትጋት ሁሉ ያለንን አድናቆት እየገለጽን ጉዳዩ እልባት አግኝቶ የሕዝቡ ጥያቄ በቂ ምላሽ እስኪያገኝ ለዚህ የሕዝብ አጀንዳ በጋራ ሕግን ባልጣሰና ሠላማዊ
በሆነ መንገድ መታገላችሁን እንድትቀጥሉ እናበረታታለን።
ኢትዮጵያንና ህዝቦቹዋን እግዚአብሔር ይባርክ።
በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (AWANA)
AWANA