ወላይታ |”ዋላሄታ”| የወላይታ ብሄር መጠሪያ ስምና የመኖሪያ ቦታ ሲሆን ትርጓሜውም የተቀላቀለ፣ የተደባለቀ፣
የተዋሀደ፣ የተቀየጠ ማለት ነው። አሁን ወላይታ በሚባልበት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ከብዙ ዘመናት በፊት ከሀገሪቱ
ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ነገዶች መጥተው በአካባቢው ከሚኖሩት ነገዶች ጋር በመዋሃድ የተመሰረተ ብሄር ነው።
በተለያየ ምክንያት ማለትም በንግድና በሌሎች ስራ ምክንያት በመምጣት ከነዋሪው ህብረተሰብ ጋር በመላመድና
በመዋሃድ ወደመጡበት ቀዬ ሳይመለሱ የቀሩና እስካሁን ድረስ የመጡበትን ብሄር ወይም ኣከባቢ ስም ይዞ ግን ወላይታ
በመሆን የሚኖር በርካታ ጎሳዎች (Clans) በወላይታ ውስጥ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ከሰሜን ትግሬና አማራ፣
ከኦሮሚያ፣ ከከፋ፣ ከጉራጌ ፣ ከሲዳማ ፣ ከጌዲኦ እና ከአማሮ ኬሎ እንዲሁም አጎራባች ከሆኑት ከጋሞ፣ ከቦሮዳ፣ ከቁጫ፣
ካዳውሮ፣ ከከንባታና ሃዲያ አካባቢ የመጡ ይገኙበታል። ይህ ጥንታዊ የሆነ የወላይታ ብሄር እስከ 19ኛው ክፍለዘመን
መባቻ ድረስ የራሱ የሆነ መንግስታዊ ስርአት የነበረዉ ሲሆን ንጉሳዊ አስተዳደርም በአካባቢው ከነበሩት መንግስታት
እጅግ ገናና ከሚባሉ አንዱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ይህ የወላይታ ንጉሳዊ ስርአት መንግስት በ19ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያን በአንድ ማእከላዊ
መንግስት ለማስተዳደር አቅዶ በተነሳው በያኔው የሸዋ ንጉስ ሚኒሊክ ጦርነት ተካሂዶበት ነበር። ይህ እልህ አስጨራሽና ደም
አፍሳሽ የሆነው ውጊያ በሁለቱ መንግስታት መካከል ለረዥም ጊዜ በበርካታ ዘሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ በመጨረሻም በጦር
አውደ ውጊያ ሳይሆን ከውስጥ በወጡ ባንዳዎች አማካኝነት መረጃ ተሰጥቶ ጦርነቱ ሊጠናቀቅ ችሏል። በእንዲህ አይነት
ሁኔታ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት አካል የሆነው ወላይታ እየዋለ እያደረ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት አምኖ
በመቀበል ለአንድ ሉአላዊ ሃገር ግንባታ ከሌሎች ብሀረስቦች ጋር በመሆን አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አበርክቱዋል፤
እያበረከተም ይገኛል። ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ደሙን አፍስሶአል፤ አጥንቱን ከስክሷል፤ ህይወቱን ሰውቷል፤ ውድ
ልጆቹን ለዳር ድንበር መከበር ገብሯል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም አብሮነትና ወንድማማችነት ከምንም በላይ
ትልቅ ዋጋ ያላቸው ነገሮች መሆናቸውን ጠንቅቆ ይገነዘባል። በተጨማሪ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ብሄራሰቦች በኢትዮጵያ
መጻኢ እድል ውስጥ እኩል ድርሻ ያለቸው መሆኑን ያለማወላወል ያምናል። ማንኛውም ብሄረሰብ በማንኛውም ሁኔታ
ከሌላው የማይበልጥ ወይም የማያንስ መሆኑን በጥልቀት ይረዳል፤ ሁሉም ብሄረሰብ እኩል መሆኑን በአጽኖት ያምናል።
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ወላይታ እንደቀደሙት አያቶቻችን ጊዜ እንደሆነው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በግልና
በመንግስት ስራ፣ በንግድና ሃብትን በማፍራት፤ በጋብቻና እንዲሁም በሰፈራ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ወገኖች
በግለሰብ፣ በቤተሰብ በድርጅትና በማህበረሰብ ደረጃ እየመጡ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት እንደሚደረገው ሁሉ
በወላይታም ይኖሩበታል። የወላይታም ህብረተሰብ የሚመጣውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን ዘር ወይም ቀለም ሳይለይ፤
ሀይማኖት፣ ጾታና የመጡበትን አካባቢ ሳይመርጥ/ሳይለይ ሁሉንም በእኩል አይን በማየት በፍቅር አስተናግዷል።
የወላይታ ህዝብ ሰው ወዳድነት እንግዳ ተቀባይነት እና ወንድማዊ ፍቅሩ ማርኩዋቸው ባህላችሁ ባህላችን ታሪካችሁ
ታሪካችን ብለው፣ ኑራቸውን ወላይታ ውስጥ ያደርጉ በርካቶች ናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የወላይታ ተወላጆችም
ከቀዬአቸው ርቀው በመሄድ በሃገሪቱ ተዘዋውረው በተለያዩ የኑሮ ደረጃ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የእለት ኑራቸውን
እየገፉ ይገኛሉ።
በዚህ አይነት ሁኔታ ከትውልድ ቀዬአቸው ተነስተው ከሄዱ የወላይታ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ አካባቢ
የሚኖሩ ይገኙበታል፤ እነዚህ ኢትዮጵያዊ የወላይታ ተወላጆች አንዳንዶቹ በአካባቢው ረዥም ጊዜን ያስቆጠሩ ሲሆኑ
ሌሎቹ እግሞ በቅርብ ጊዜ በስራ ምክንያት የሄዱ ናቸው። እነዚህ ወገኖች ሰላማዊ ኑራቸውን እየመሩ ከአካባቢው
ህብረተሰብ ጋር በሰላም ወጥተው በሰላም ገብተው በማንኛውም ሁኔታ የአካባቢው ህብረተሰብ ስጋት ሳይሆኑ የሰላምና
የፍቅር አጋር ሆነው በአብሮነትና ወንድማማችነት በኢትዮጵያዊ ባህል እየኖሩ የእለት ተእለት ስራቸውን የሚያከናውኑ
ናቸው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ብሄረሰብን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየደረሰባቸው
እንደሆነ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ከአካባቢው የሚመጡ የአይን ምስክሮችና የጥቃቱ ሰላባ
የሆኑት ወገኖች ከሚናገሩት ለማወቅ ተችሏል። ይህ ድርጊት እጅግ ዘግናኝ የሆነና አሳዛኝ ነው። በዚህም ልባችን በጣሙን
አዝኗል። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉና ሰባዊ ፍጡር ሁሉ ያዘነበትም ነው፤ ሊወገዝም የሚገባው ነው።
እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያዊ የሆንን የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ይህንን ክስተት ስንሰማ
በድንጋጤ ተውጠን ምን እየተደረገ ነው? ወዴት እየሄድን ነው? ብለን እራሳችንን እንድንጠይቅ አስገድዶናል። የወላይታ
ተወላጅ የሆነ ግለሰብ፤ እንድማንኛም ኢትዮጵያዊ ኦሮሚያ ዝዋይ አገሩ እንደሆነ እናምናለን፤ እንዲሁም ጎንደርም
ጎጃምም፣ ጂማ፣ ሀረርጌ፣ ሶማሌ ወዘተ አገሩ ነው። ነገር ግን የወላይታ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ ምንም አይነት
ምክንያት ሊቀርብበት በማይችል ሁኔታ ለብዙ ዘመናት ከኖረበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ ሲደረግ፤ ህጻናትና አቅመደካማ
አዛውንቶች ድብደባና እንግልት ሲደርስባቸው፣ ቤታቸውና ንብረታቸው ሲቃጠልና ሲወድም፤ ሰዎች በግፍ ሲገረፉና
ሲገደሉ መስማት በጣም ያማል። ከዚህም አልፎ ተርፎ የአስተዳደር በደል ደረሰብኝ፣ ፍትህ ተንፈግኩኝ፣ ሙስና
በመንሰራራቱ አገር መልማት አልቻለችም በማለት በህዝባዊ አመጽ ተቃውሞን እየገለጸ ያለው የኦሮሚያ ወጣት የህዝብ
ማመላለሻ መኪናዎችን የመንግስት የግል መኪናዎችን እያስቆመ ወደ ውስጥ በማስገባት “ወላይታ አለ?” እያለ ለግልና
ለመንግስት የስራ ጉዳይ እንዲሁም ለማህበራዊ ጉዳይ በዝዋይና ሻሸመኔ አካባቢ በማቋረጥ የሚመላለሱትን የወላይታ
ተወላጆችን እያወረዱ ድብደባ እንግልትና ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሆን እየተነገረ ነዉ። በጣም የሚገርመው ደግሞ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለህዝቦች አንድነትና እኩልነት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቆርጬ ተነስቻለሁ እያለ
በሚሰብክበት ጊዜ ይህ ሁኔታ መፈጠሩ ነው። ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ አትዮጵያዊነት አማራ ብቻ
አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት ወላይታም ጭምር ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ሁሉንም ብሄር የሚጨምር ነው። ሙሉና ግማሽ
ኢትዮጵያዊ የለም፤ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን እንደሆነች እናምናለን።
ስለዚህም እኛ በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆንን የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ከሌሎችም በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ
ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመወያየትና በመመካከር የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸዉ ሁሉ
በአክብሮት እናቀርባለን።
- የወላይታ ተወላጆች እንደማንኛም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመስራት፣ ሀብት የማፈራት እና
በሰላም የመኖር ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ፤ - የኦሮሚያ መስተዳደር ወንጀለኞቹን ለፍትህ የማቅረብ ስራውን በፍጥነትና በሙሉ ፍትሃዊነት
እንደሚያጠናቅቅ ተስፋ እያደረግን ውጤቱ ለተጎጂውም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ በይፋ በመገናኛ ብዙሃን
እንዲገለጽ ፤ - ለሞቱት የወላይታ ተወላጆች ቤተሰቦች አግባብ ያለው ካሳ እንዲከፈል፣ ቤትና ንብረት ለተቃጠለባቸው
ለተዘረፈባቸው ተገቢ ካሳ እንዲከፈላቸው ፤ - የፌደራል መንግስት የኦሮሚያ መስተዳደር የደቡብ ብሄር መስተዳደርና የወላይታ ዞን አስተዳደር ይህን ጉዳይ
በሃላፊነት የሚከታተል ቡድን ፈጥሮ ሂደቱንና ውጤቱን ለመላው የደቡብ ህዝብ ለመላው የኦሮሞ ህዝብ፤
እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር ይፋ እንዲያደረግ በአክብሮት እንጠይቃለን።
እግዚኣብሔር ኢትዮጵያን ይባርካት!
በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር።
AWANA