በወላይታ ሕዝብ ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃና መሠረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር-AWANA Date: 8/11/2020

በወላይታ ሕዝብ ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃና መሠረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር-AWANA 8/11/2020
******************************************************
ካለፈው ዕሁድ ጀምሮ መንግሥት በወላይታ ሠላማዊ ሕዝብ ላይ እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃና እሱንም ተከትሎ የፈሰሰውን የንጹኃን ወላይታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በግፍ መገደል በታላቅ ሐዘንና የልብ ስብራት እየተከታተልን ነው። በወላይታ ሕዝብ ላይ ይህ አስደንጋጭ የግፍ እርምጃ እየተወሰደበት ያለው በክልል ደረጃ ራስን በራስ የማስተዳደር መዋቅራዊ ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል። የወላይታ ሕዝብ ይህንን ጥያቄ ካቀረበበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ሲታገል መቆየቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን መንግሥት በቸልተኝነት ሕግንና ሕጋዊነትን ባለማክበር ሕዝቡን ሲያፍን መቆየቱን በተግባር ሲያሳይ ቆይቶአል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አንጻራዊ በሆነ ለውጥና ሽግግር ላይ ትገኛለች። የወላይታ ሕዝብ በዚህ የሽግግር ወቅት ብዙ ዋጋ የከፈለና ብዙም መከራ የተፈራረቀበት መሆኑ የሚታወስ ነው።

የወላይታ ሕዝብ ይህንን የክልልነት ጥያቄ ያነሳው በስሜታዊነት ተነሳስቶ ወይም የሌሎችን ፈለግ በመከተል ብቻ ወይም እንደሚባለው ከሌሎች ሀይሎች የተሰጠ የቤት ሥራ አድርጎ ሳይሆን በተደጋጋሚ የደረሰበትን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ጭቆናና በደል ለመግፈፍ፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር የልማት መሠረታዊ መብት ለመጠቀም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ የደረሰበትን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት (ሞት፣ መፈናቀል፣ በቁም ሰዎች የተቃጠሉበት፣ ሕጻናት በዱላ ተቀጥቅጠው የተገደሉበትና አስክሬናቸው በመሬት የተጎተተበት) ግፍና በደል መቃወምን መሠረት ያደረገ መሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያንና መላው ዓለም የታዘቡት ነው።

ይህንን ሠላማዊ የሕዝብ ጥያቄ ከተለያዩ የአገሪቱን ለውጥና ዕድገት ከማይፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች ጋር በማያያዝ መንግሥት እየሄደበት ያለውን አቅጣጫ እንዲያርም በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር አባላት በዛሬው ዕለት Aug 10,2020 ባደረግነው ጠቅላላ ጉባዔ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ባለ ስምንት ነጥብ መግለጫ አውጥተናል።

1. የወላይታ ሕዝብ ሕግንና ሕጋዊነትን ተከትሎ በሠላማዊ መንገድ ብቻ ጥያቄውን አቅርቦ በትዕግሥት እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ በሕዝቡ ዘንድ ምንም ዓይነት አመጽ ሳይታይበት መንግሥት ሠላማዊ በሆኑ ዜጎች ላይ ሕጻናትን ጨምሮ በመግደል የከፈተውን አጠቃላይ የኃይልና የሽብር እርምጃ እያወገዝን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያቆም እንጠይቃለን።

2. በዚህ ሰብኣዊነት በጎደለውና አሰቃቂ ሁኔታ አካላቸውን ለተጎዱት ፈውስን፣ በጭካኔ ለተገደሉት እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት እንዲያኖርልን እየተማጸንን ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የወላይታ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን።

3. ከተለያዩ ምንጮች እንደተሰማውና መንግሥትም እንደገለጠው በዚሁ ወቅት ታፍሰው የታሠሩ አካባቢውን እያስተዳደሩ የሚገኙ የሕዝብ መሪዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች፣ የወጣቱን ክንፍ የሚመሩት ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።

4. መንግሥት ማንኛውንም መሠረታዊና ወቅታዊ የሕዝብ ጥያቄ በኃይል እርምጃ ሳይሆን ከሕዝቡና ከሕዝቡ መሪዎች ጋር በቅርበት በመመካከር ፍትሓዊና ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚገባ መሆኑ ታውቆ የሰውን ሕይወት ከማጥፋትና ሕብረተሰቡን አላስፈላጊ ሽብርና ሁከት ውስጥ ከማስገባት ተቆጥቦ ሕዝቡ ለጠየቀው ሕጋዊ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ በአጽንዖት እንጠይቃለን።

5. የወላይታ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ደሙን ያፈሰሰና አጥንቱን የከሰከሰ ሕዝብ መሆኑና ዛሬም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑ ታውቆ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋ በማስመሰል በሕዝቡ ላይ ጥላሸት የሚቀቡ ሁሉ ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።

6. በወላይታ ውስጥ አሁን የተከሰተውን ሁኔታ በመጠቀም እውነታውን በማዛባት በተለያዩ ሚዲያዎች አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በሕዝቡ ላይ እያደረሱ የሚገኙትን ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን።

7. ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኙ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦችም ሆነ መላው ሠላም ወዳድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ፣ የተለያዩ የሚዲያ ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በወላይታ ሕዝብ ላይ በገዛ አገሩ በመንግሥት እየደረሰበት ያለውን ጥቃት በደልና ግፍ አብረውን እንዲያወግዙ ጥሪ እናቀርባለን።

8. በመጨረሻም በመላው ዓለም የሚገኙ ጠቅላላ የዲያስፖራ አባላት በወላይታ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል በጋራ እንድትቆሙ ይህ ታላቅ ግፍና መከራ እየደረሰበት ላለው ወገናችሁ የምትችሉትን ድጋፍ ሁሉ እንድታደርጉና ድምጻችሁን እንድታሰሙ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ሠላምን ይስጥ!! #Wolaita #Ethiopia #Ethiopian Government Must Stop Attacking Innocent people of Wolayta!

Leave a comment