COVID-19 GoFundMe ን በተመለከተ ከአዋና የተሰጠ መግለጫ

በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (AWANA) በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነው COVID-19 በወላይታ አካባቢ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ድጋፍ ከመላው አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን በGoFundMe አማካይነት ስንሰበስብ መቆየታችን ይታወሳል።

በተለያዩ ጊዜያት በመላው አገራችን ሲከሰት በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት በተለይም ደግሞ በነሐሴ ወር በወላይታ በፌደራል መንግሥት ወታደራዊ ኃይል በንጹኃን ላይ የተወሰደው ጥቃት ካስከተለው አለመረጋጋት የተነሳ ፈንዱን ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ ለማውረድ ምቹ ሁኔታዎችን ማግኘት ባለመቻላችን ለተወሰነ ጊዜ መዘግየት እንደገጠመን ካሁን በፊት መግለጻችንም አይዘነጋም።

በአሁኑ ሰዓት ከዞኑ አስተዳደር ተወካዮች፣ ከጤና መምሪያ ተወካዮች እንዲሁም ሥራውን በበላይነት እንዲከታተሉ ከአዋና በኩል ከተመረጡት ተወካዮቻችን ጋር በመሆን በጥምረት የተቋቋመው ኮሚቴ አስቀድሞ በተቀረጸው ፕሮጀክት ፕላን መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ የስምምነት ውል በመፈራረም ወደ ሥራው ተገብቶአል።

በዚሁ መሠረት ሥራውን እንዲያሳልጡና አፈጻጸሙን በበላይነት እንዲመሩ አቶ አሳምነት አይዛ፣ አቶ ላቀው ዋልቶሬ፣ አቶ ተስፋዬ ፈለሃ፣ አቶ አንዱዓለም ሰይድና ወ/ት እንጉዳይ መስቀለ በጥምረት ኮሚቴነት ተሰይመው ገንዘቡ ከGoFundMe ወጪ ተደርጎ ሊላክ ችሏል።

በፕሮጀክት ፕላን እንደተገለጸውና በስምምነት ውሉም ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ሥራው ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተወከሉ አካላት አማካይነት በውጤታማነት ሊሠራ የተጀመረ መሆኑን ለውድ አባሎቻችንና ወዳጆቻችን እየገለጽን የስምምነቱን ውልና የፕሮጀክቱን ፕላን ኮፒ እንዲሁም ገንዘቡን የላክንበትን ደረሰኝ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ አድርገን መላካችንን እናስታውቃለን።

የሥራውን ሂደት እስከፍጻሜው እየተከታተልን በየጊዜው የምናስታውቃችሁ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እንጠቁማለን።

እግዚአብሔር ሃገራችንንና ህዝቦቿን ይባርክ!!

Leave a comment