በመስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም አቶ መሳይ መኮንን ይመራ በነበረው “ዕለታዊ” በተሰኘው የኢሳት መርሃ ግብር ላይ ስለ ብሔርተኝነት በተነሳው ሐሳብ አቶ ግዛው ለገሰ ስለ ወላይታ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ አስታውሰው መጥፋትና መሸነፍ ያለበት መሆኑን መናገራቸው በወላይታ ሕዝብ ዘንድ ቅሬታ፣ ጥያቄና ቁጣን የጫረ ተግባር ሆኗል።
ከኢሳት ስቱዲዮ ካሁን ቀደምም እንዲህ ዓይነት የወላይታን ሕዝብ ዒላማ ያደረጉ ሕዝቡን ከሌላ ወንድም ሕዝብ ጋርና ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት ሆን ተብለው የተሸረቡ የሚመስሉ ዝግጅቶች አየር ላይ ሲውሉ የነበረበትንም ሁኔታ የምንዘነጋው አይደለም።
የወላይታ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመሆን የአገሩን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ እንደ ሁል ጊዜውም የሕይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ የትኛውንም ዋጋ እየከፈለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት በሬ ወለደ ክስ በመላው የወላይታ ሕዝብ ላይ ማንሳት “ሠላም ወዳድ ነኝ የአገርን አንድነት እፈልጋለሁ” ከሚሉ ግለሰቦች ኢሳትን በሚመስል ታዋቂ ሚዲያ አማካይነት መለቀቁ በእውነቱ የሚያስተዛዝብና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው።
የወላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያን አንድነት ሊፈታተን በሚችል መልኩ አክራሪ ብሔርተኞች በሚሸርቡት ሴራ ለአንድ አፍታም ሳይወዛገብ ለኢትዮጵያዊነትና ለሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም በመታመን አሁን ሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የመደራጀትና የመልማት መብቱን መጠየቁ የታወቀ ነው። ይህም እየሆነ ያለው የወላይታ ብሔር እንደ ሌሎቹ የአገራችን ብሔሮች የራሱን ባሕል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ የማሳደግ ተፈጥሮአዊ መብት ለመጠቀም ሲል መሆኑም መታወቅ አለበት። ይህ መብቱ እንዳይከበርለት የሚደረገውን የትኛውንም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት የማንቀበለው መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን።
አቶ ግዛው ለገሰ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ የጋዜጠኝነትንም ሥነ ምግባር በማይመጥን መልኩ እንዲህ ያለ ግብረ ገብነት የሌለውን ንግግር በመላው የወላይታ ብሔር ላይ በመናገሩ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር ቅሬታውን በፕሬዚዳንቱ አማካይነት በሕጋዊ ደብዳቤ ለኢሳት ቢሮ በማድረስ ምላሹን እየተጠባበቀ የሚገኝ መሆኑንም ለማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች መግለጽ እንወዳለን።
የኢሳት ቢሮ እንዲህ ያሉ የሕዝብን ቁጣ የሚያነሳሱ፣ መንግሥትንም በሕዝብ ላይ ያለ አግባብ ሊቀሰቅሱ የሚችሉ የሽብር ተግባራትን የሚፈጽሙ ጋዜጠኞችን የማረም እርምጃ በመውሰድ ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የድርጊቱ ፈጻሚውም ሆነ ሚዲያው ክቡር በሆነው የወላይታ ሕዝብ ላይ ያለአግባብ የተደረገውን ዘመቻ በሚመለከት ግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (Awana Wolayta) ያሳስባል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
መልካም አዲስ ዓመት!!
በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (AWANA – Wolayta)
AWANA