በወላይታ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰትና አፈናን በተመለከተ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (AWANA) እና በዋሽንግተ ዲሲ አካባቢ የወላይታ ኅብረት (WCDC) በጋራ
August 9, 2022

ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው የወላይታ ብሔር በኢትዮጵያ ታሪክና አገር ግንባታ ሂደት ከሌሎች የአገራችን ህዝቦች ጋር ኢትዮጵያን በማልማት፣ አንድነቷንና ሉአላዊነቷን በማስከበር ረገድ የሕይወት መሥዋዕትነት ሁሉ እየከፈለ የኖረ ኩሩና አገር ወዳድ ሕዝብ መሆኑን ማንም አይክደውም።

አገራችንን ከፀረ-ሠላም ኃይሎች ለመታደግ እንዲሁም ሠላሟንና ጸጥታዋን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የወላይታ ሕዝብ ገንዘቡንና ጊዜውን ብቻ ሳይሆን የልጆቹንም ደም የገበረ የአገርን መደፈር አጥብቆ የሚጠላ ብርቱ ሕዝብ መሆኑን ማስረዳትም አያስፈልግም።

ሆኖም ግን በየዘመናቱ የተነሱት የኢትዮጵያ ገዢዎች ለህዝቡ የሚመጥን ሥርዓት ከመዘርጋት ይልቅ በተቃራኒው አስተዳደራዊና መዋቅራዊ በደልና ጭቆና ሲያፈራርቁበት ኖረዋል። በዚህም ምክንያት በነፃነትና እኩልነት ለመኖርና ለመዳኘት የነበረው የሕዝብ ፍላጎት እስከ ዛሬ መክኖ ቀርቶአል። ለዚህ ብዙ ማሳያዎች አሉ።

ለምሳሌ ያህል:- ሕወኃት በምትመራው የኢህአዴግ ዘመን የወላይታንና የአካባቢውን ሕዝብ ባሕልና ቋንቋ፣ የአኗኗር ወጉንና ሥርዓቱን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ታቅዶ ለግል ጥቅማቸውና ሥልጣናቸው ቅድሚያ የሚሰጡ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የወላይታ ተወላጆችም ጭምር በመጠቀም በየትኛውም ዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አፋኙ መንግሥት ሕዝቡን መግቢያ መውጫ አሳጥቶ የብዙዎችን ደም አፍስሶና በርካታዎችን አስሮና ከቤት ከንብረቱ አፈናቅሎ የነበረ ቢሆንም በወላይታ ሕዝብ ቁርጠኛ ትግል ጥረቱ መቀልበሱ የሕዝባችን የቅርብ ጊዜ ትዝታው ነው።

“ወጋጎዳ” የተባለውን ድብልቅ ባሕልና ቋንቋ በሕዝብ ላይ በመጫን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ያስቆጡት፣ ኢፍትሓዊ ድርጊት በሕዝቡ ላይ የፈጸሙት የጊዜው ካድሬዎች ለፍትሕ ሳይቀርቡ፣ በገዛ ወገናቸው ላይ ላደረሱት በደልና ግፍ ሳይጠየቁ የታለፉ ከመሆናቸውም በላይ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች እስከ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ተሹመው የነበረ መሆኑም አይዘነጋም። ያንን ሁሉ ድርጊት በሕዝባችን ላይ የፈጸሙት ግፈኞች በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስገው ሕዝባችንን አሳር ሲያበሉ የኖሩ ሲሆን ለዛሬውም የሕዝባችን መከራ እጃቸው እንዳለበት ይታመናል።

ከአንድ ዓመት በፊት ብልጽግና በሚመራው የለውጥ መንግሥት ደግሞ “የክልል ጥያቄ አጥብቃችሁ ለምን ትጠይቃላችሁ?” በሚል ምክንያት ብቻ በሶዶ እና በቦዲቲ ከተሞች በንጹኃን ዜጎች ላይ ከፌደራልና ከደቡብ ክልል መንግሥታት በተላኩ ታጣቂዎች የዘነበባቸው ጥይት የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፎአል። ለዕለት ጉዳያቸው ወጥተው መንገድ ዳር የነበሩ እርጉዝ ሴትን ጨምሮ በርካታ ሕጻናትና ሰላማዊ ሰዎች በዚሁ ወቅት በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የወላይታ ሕዝብ እንደሌሎቹም የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም በማያወላዳ አቋም ክልል የመሆን ጥያቄ አቅርቦ በዞኑ ምክር ቤት አስወስኖ እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ምላሽ ሲጠባበቅ ቆይቶአል። ይህንን ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄውን ሕዝቡ በሠለጠነና ፍጹም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ሲጠይቅ የነበረ ቢሆንም በመንግሥት በኩል የተለያዩ ትንኮሳዎች ሲደርሱበት እንደነበር ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። የወላይታ ሕዝብ በሌሎች አካባቢዎች እንደታየው የሌላ አካባቢ ተወላጆችን ያሸማቀቀበት፣ ብሔር ለይቶ ያፈናቀለበት ያሳደደበት፣ የገደለበት ቀን ያልነበረ መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የወላይታ ሕዝብ እየጠበቀ የሚገኘው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ሆኖ ሳለ የሕዝቡን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ለመረዳት በሚከብድ ፍጥነትና አኳኋን በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ውሳኔ ሰጪነት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ውሳኔ ተደርጎ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መቅረቡ ተሰምቶአል። ይህ ሕዝቡን ያፈነና የብልጽግና ካድሬዎች እንጂ የሕዝቡን ይሁንታ ያላገኘ ውሳኔ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና አላቸው ከሚባሉት ሕዝቦች ጋር ለመጨፍለቅ ብርቱ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

ይህም አሠራር “አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ዓይነት ከመሆኑም በላይ ይኼኛው መንግሥት ካለፉት መንግሥታት ስሕተቶች ምንም ትምህርት ያላገኘ መሆኑን አመላካች ነው። ይህ አፋኝ ውሳኔ የወላይታን ሕዝብ መብትና ጥቅም ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የአካባቢውን ሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት የገፋ መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የወላይታ ተወላጅ ዲያስፖራ አባላት የወላይታ ሕዝብ ሕግንና ሥርዓትን ተከትሎ ያቀረበውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለማዳፈን የሚደረገውን መንግሥታዊ አፈና በተመለከተ በሁለቱ ድርጅቶች በኩል ከዚህ በታች ያለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

  1. የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ የክልልነት አደረጃጀት ሆኖ ሳለ ሕገ መንግሥቱ የማያውቀውን “ክላስተር” የተባለውን አደረጃጀት በማምጣት የሕዝቡን ፍላጎት ለማፈን ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ውስጥ የተገባበት ሁኔታ በወላይታ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እየገለጽን በካድሬ የተፈበረከው “ክላስተር” የተባለው መዋቅር ኢሕገ-መንግሥታዊ በመሆኑ ይህንን ድርጊት የሚፈጽመው አካል በሕዝብም በታሪክም የሚጠየቅ መሆኑን አውቆ ከዚህ የጥፋት መንገዱ እንዲመለስ እናሳስባለን።
  2. የወላይታ ሕዝብ ይህንን የክልልነት ጥያቄውን በየቀበሌያትና በየወረዳዎች ሁሉ አስወስኖ በስተመጨረሻም በዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ጸድቆ ለደቡብ ክልልና ለፌደሬሽን ምክር ቤት የተላከ ሕዝባዊና ሕጋዊ ውሳኔ ወደ ጎን ተደርጎ በአሁኑ ጊዜ ከላይ ወደታች አዲስና አስደንጋጭ ውሳኔ በሕዝቡ ላይ መጫን የሕዝቡን ሉዓላዊነትና ሕጋዊ መብት መጋፋት መሆኑ ታውቆ ሂደቱ እንዲቋረጥ እናሳስባለን።
  3. የወላይታ ሕዝብ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች በመሳተፍ የበኩሉን ኃላፊነትና ግዴታውን እንዲወጣ የሚጠበቅበትን ያህል እንደ ዜጋ የሚጠይቃቸውን ሕጋዊ መብቶችን ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚደረገውን የትኛውንም የገዢውን ፓርቲና መንግሥት መዋቅራዊ አፈና እንቃወማለን።
  4. የወላይታ ሕዝብ ይህንን የመብት ጥያቄውን እንዲያቆም ለማድረግ ከየአቅጣጫው የሚነዙትን የማሸማቀቂያ ዘዴዎችን “ክልል መጠየቅ ዘረኝነት ነው”፣ “ጠባብነት ነው”፣ “ጎጠኝነት ነው መታጠር ነው”፣ “ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው” የሚሉትና ሌሎችንም አጓጉል ትርጓሜዎችና አባባሎች ጊዜ ያለፈባቸው ስልቶች መሆናቸው ታውቆ እንዲቆሙ እናሳስባለን።
  5. በተለያዩ የአገራችን ክልሎች ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ፣ በየዕለቱ እንደ በግ ሲታረዱ፣ በገዛ አገራቸውም የመኖር መብታቸውን ሲገፈፉ፣ መከላከልና ሕጋዊ ከለላ ሊሰጥ ያልቻለ ብልጽግና መራሹ መንግሥት ፍጹም ሠላማዊ የሆነውን ሌሎችንም ወንድም ኢትዮጵያውያንን አቅፎ የተቀመጠውን ሕዝብ ከማሸበር ተግባሩ እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
  6. እየፈረሰ የሚገኘው የደቡብ ክልል መንግሥት ትክክለኛውን የሕዝብ ጥያቄ ወደ ጎን በማድረግ “በሳይንሳዊ ጥናት እናዋቅራለን” ሲል ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ በክላስተር እናደራጃለን በሚል ውሳኔ ከተሞችን እንደዚህና እንደዚያ እናደርጋለን በሚል መደለያ ጭምር ለዘመናት በመተሳሰብና በአጋርነት የኖረውን አጎራባች ሕዝብ እርስ በርሱ ለማጋጨት ከሚያደርገው ኃላፊነት ከጎደለው ተግባሩ እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
  7. በመጨረሻም ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ የጠየቀው መሰረታዊ የመብትና የእኩልነት ጥያቄ በፍትሃዊ መንገድና በእዉነተኛ መግባባት እስካልተፈታ ድረስ አከባቢው ላልተቋረጠ የመብት ትግል ውጥረትና ቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ በፍትዊነትና እኩልነት የሚያምን ሃገር ወዳድ ኢትዮዽያዊ ሁሉ ሊያሳስብ የሚገባና የሚወገዝ ተግባር መሆኑንም እናሳስባለን።

Leave a comment