Dama godda (ባለዳማዉ ፈረስ) ኣቶ ኣየለ ኣዳሬ በመሞታቸው የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።

Dama godda (ባለዳማዉ ፈረስ) ኣቶ ኣየለ ኣዳሬን ከልጅነቴ ጀምሮ የማዉቀዉ “ምኖ ጎባ ኣሳ” (የተሳካለት ጎበዝ ሰዉ) ተብሎ ነዉ። በዚያን ጊዜ የማዉቀዉ ግን የተዋጣለት የስራ ሰዉ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በግርማ ሞገሱ ፈገግታዉ ቀልዱና በምክሩም ስፍራን የሚሞላ ሰዉ ነበር። ፈረንጆች “larger than life itself” የሚሉት አይነት ሰዉ።

የኣደባባይ ብቃቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ወላይታም ኢትዮጵያም ልክ እንደ ኣሁኑ ወቅት በከባድ ድባብ ዉስጥ በነበሩበት ወቅት ነበር። በኢትዮጵያ ኣቆጣጠር 1984 ዓ/ም ወይም 1985 ዓ/ም ክረምት ላይ። በወላይታና አከባቢዉ በወቅት ስለነገሰዉ ዉጥረት ተነጋግሮ ዉሳኔ ላይ ለመድረስ በሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትም/ ቤት አዳራሽ ታላቅ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር። ያኔ ወህዴድና ወህዴግ በሚባሉ የወላይታ ፓርቲዎች መካክል የነበረዉ የለየት ጦርነት የስብሰባዉ ባክግራዉንድ አካል ነበር።ነፍሱን ይማረዉና በአቶ ተፈራ መስቀሌ የሚመራዉ ወህዴድ በኢሃደግ መራሹ ፈደራል መንግስት ከፍተኛ ድጋፊ በአከባቢዉ ፖለቲካ የበላይነትን አግኝቶ ስልነበረ የስብሰባዉ አዘጋጆች እነሱ ነበሩ። ሁሉንም ሰዉ ግን ጋብዘዋል (to their credit)። Everybody who was somebody in Wolaita society የተገኘበት ይመስል ነበር። አዳራሹ አፍንጫዉ ድረስ ሞልቱል። ብዙ የፖለትካ አዋቂዎች የፓርቲ አለቆች የተማሩ ሰዎች የዚህም የዚያም ተወካዮች ብዙ ካወሩ በኋላ ከመሃክል ለአንድ የሃገር ሽማግሌ አባት ማይኩ ተሰጣቸዉ (ለአቶ አየለ አዳረ)።

የሆነ አይነት ዜማ ያለዉ በሚመስ ንግግር ለጥቂት ሰኮንዶች ማዉራት እንደጀመሩ ሰማይ ምድር ፀጥ ብሎ የሚያዳምጥ እስኪመስል አዳራሹ በታላቅ ፀጥታ አዳመጣቸዉ። ስለታሪካችን ስለአከባቢያችን ስላለፉ የሃገራችን መሪዎችም ስለጥሩነትና ክፋት በጥቂት ደቂቃዎች እጅግ ብዙ አስተማሩን። ከብዙ ምክራቸዉ ትንሽ ለማስታወስ”…ከፍ ያላችሁ ከናንተ በታች ያለዉን በጫማችሁ አትርገጡ፤ ጣቶቻቸዉን ይዛችሁ ወደላይ ሳቡዋቸዉ። ከታች ያላችሁ እናንተም ትንሽ ከፊ ያለዉን ሰዉ በክፋት መንፈስ ወደታች አትጎትቱ፤ በትከሻችሁ ወደላይ ደግፉዋቸዉ (ካፍተ)። እሶይ እሱዋ ጫዶፕተ…” ብዙ የሚስተምር ነገር ስላላቸው ስለሙሉ ታሪካቸዉ አንድ ቀን እናነብ ይሆናል።

ዳማ ጎዳ አቶ አየለ የህዝብ እንደራሴም ሆነዉ ነበር። በኋላም ከደኢህደን ካድረዎች ጋር ተጋጭተዉ ታስረዉም ነበር። በሃገር አቀፍ ደረጃ ሞደል ገበሬ ሆነዉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሽልማት ካገኙ ጥቅት ኢትዮዽዊያን አንዱ ነበሩ። ለአክባቢዉ ልማት ጉልህ ሚና ተጫዉተዋል። የክርስትና ህይወታቸውና የቤተሰብ አስተዳደራቸዉ በሃገር የተመሰከረላቸዉ ነበር። መጥፎ ነገርንና ክፋትን በብርቱ ይፀየፉ ነበር። ከእግዚሃብሄር በስተቀር ማንንም ሳይፈሩ እዉነት የመሰላቸዉን ነገር ድምጻቸዉን ከፍ አድርገው ሲናገሩ ኖረዋል።

ዳማ ጎዳ አቶ አየለ አዳረ ባለው አክባቢያዊ ሁኔታ ብዙ ተፅዕኖውችን ተቁዋቁመዉ ታላቅ ገድልን ተጋድለው መልካም ህይወት ኖረዉ የልጅ ልጅ አይተዉ የሰዉ ፍቅርና አክብሮት ሳይለያቸ ያረፉ ታላቅ የወላይታ ተወላጅ ኢትዮጽያዊ ነበሩ። ወደዘለአለሙ አለም ማለፋቸዉ ለርሳቸዉ እረፍት ቢኖንም ለሚዉዷቸዉ ሁኑ በስጋ ለባሽነታችን ጥልቅ ሃዘን ነዉ።
ለመላዉ ቤተሰብ ዘመድና ወዳጅ በራሴና በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆት ማህበር ስም እግዚሃብሄር ያፅናናችሁ እላለሁ።

ፕሮፌሰር ዳታ ዴአ
በሰሜን አሜሪካ የዎላይታ ተወላጆችና ወባጆች ማህበር ፕሬዚዳንት

Leave a comment