በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር በወላይታ ህዝብ ላይ በክልል መዋቅር ጥያቄ ምክያት እየደረሰ ስላለው ሕገ-መንግሥታዊና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ October 17, 2020

እንደሚታወቀው በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክና አገር ግንባታ ሂደት የወላይታ ብሄር ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን አገሩን በማልማትና በመገንባትና ሉአላዊነቷን በማስከበር ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ውድ ህይወቱን የከፈለ፤ እየከፈለም የሚገኝ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር፤ ጠንካራ፤ ሥራ ወዳድ እንድሁም ሰውን በዘሩ ሳይሆን በሰውነቱ (በሰብአዊነቱ) የሚወድ ኩሩ ህዝብ ነው ፡፡

ይሁን እንጅ በአጼዎቹ፣ በደርግና በኢህአደግ ዘመነ መንግስታት የየዘመኑ ገዥዎች ሆን ብለው አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ጫና በማድረግ የወላይታ ህዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ መልማት በሚገባው ልክ እንዳይለማ፤ የፍትህና የመልካም አስተዳደር ተቋዳሽ እንዳይሆን በረቀቀ መንገድ ሲጨቁኑ ኖረዋል፡፡ ሕዝቡ ከዚህ ጭቆና ለመላቀቅ ለረጅም ዘመናት ሲታገል የቆየ ሲሆን በተለየም ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት መላው የወላይታ ህዝብ ፍጹም ሰላማዊ፣ ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲዊ በሆነ መንገድ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን በጨዋነትና በሰለጠነ መንገድ ሲጠይቅ እንደነበረ እውነተኛ ህሊና ያላቸው የሃገራችን መሪዎችና መላው የኢትዮጵያ ህዝብም የሚያውቁት ሐቅ ነው።

ነገር ግን የፈደራልና የፈራሹ ደቡብ ክልል መሪዎች የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ክብርና የሞራል ከፍታ በማይመጥን፣ ለሃገሩ ግንባታና ለዳር ድንበሩ መከበር የከፈለውን ዋጋ ባለመገንዘብ፣ ፍጹም ሃሰት በሆነ የፈጠራ ትርክት የህዝቡን ህጋዊና ግልጽ ጥያቄ እንደመመለስ “የወላይታ ህዝብ ከጸረ ሰላም ሐይሎች ጋር ግንኙነት አለው” በማለት በርካታ ንጹሐን እንዲሞቱ፣ እንዲቆስሉና የትግሉ መሪ የዞኑ አመራሮች በግፍ እንዲታሰሩ አድርገዋል። በተጨማሪም ለህዝቡ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠትና በመረጧቸው መሪዎች እንዲመሩ በማድረግ ውጥረቱን ማርገብ ሲቻልነገር ግን መንግስት በከፋፍለህ ግዛ መንገድ የህዝቡን ሰላማዊ የመብት ትግል በታጠቁ የፈደራልና ክልል ጦር ኃይል በማፈን፣ ወጣቶችን በማሰርና በማሳደድ፣ ህዝቡ እርስበራሱ እንዲጠራጠር፣እንድሁም አከባቢው ተረጋግቶ ህብረተሰቡ በልማት ስራ ላይ እንዳያተኩር እያደረገ ይገኛል።

እንደዚሁም አስፈላጊ መስፈርቶች ሁሉ ተማልተው በዞን ም/ቤት ጸድቆ በክልል ም/ቤት አለአግባብ በመታፈኑ ፟ይግባኝ የቀረበለት ፈዴረሽን ም/ቤትም በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ ሃላፍነቱን ያለመወጣቱ ችግሩ ተፈትቶ በአከባቢው የሰላም አየር እንዳይነፍስ ከማድረጉም በላይ የመብት ጥሰቶች እንዲባባሱ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በመሆኑም እኛ በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር አባላት በዛሬው ዕለት October 17, 2020 ባደረግነው ጉባኤ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ባለ፟ 9 ነጥብ መግለጫ አውጥተናል።

1 የወላይታ ህዝብ ህግንና ስርዓትን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን አቅርቦ በትዕግስት እየተጠባበቀ ያለውን በክልል የመደራጀት የመብት ጥያቄ በአስቸካይ ምላሽ እንዲሰጥ፤

2 የመላውን ወላይታ ህዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እያስተጋቡ በመንግስት ስራ ላይ እያሉ በሐሰት የፈጠራ ወንጀል ተጠርጥረው አለአግባብ የታሰሩ የቀድሞ ዞን አመራሮች፣ የንግዱማኅበረሰብ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ወጣቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤

3 በሠላማዊነቱና በጨዋነቱ የማይታማውን፣ ግዴታውንና መብቱን በማወቅ ባዶ እጁን ለሰልፍ የወጡ ንጹሀን እንዲጨፈጨፋ ባዘዙት፤ ባስፈጸሙትና በፈጸሙ የፈደራል ይሁን የክልል አመራሮች እንድሁም ያልተመጣጠነ ኃይል በተጠቀሙ የጸጥታ አካላት ላይ ተገቢው ምርመራ ተጣርቶ ለህግ እንዲቀርቡ፤

4 ያለ ጥፋታቸውና ወንጀላቸው በመንግስት ጦር ተጨፍጭፈው ህይወታቸውንና አካላቸውንላጡ ተገቢው ካሣ እንዲከፈል፤

5 የክልል መዋቅር ጥያቄ ለቅንጦት ወይም ለፉክክር አሊያም ለጥቂቶች ሥልጣንና ጥቅም ሳይሆን ለዘመናት ያለፍላጎቱ በተጫነበት ኢ-ፍትሔዊ የአስተዳደር አከላለል ምክንያት ታታሪውና ሥራ ወዳድ ህዝባችን በከፋ ድህነት ውስጥ በመሆኑ ማንነቱን፣ ባህሉንና ቋንቋውን በተገቢው ማሳደግ ባለመቻሉና በሌሎችም በርካታ ተጨባጭ ገፊ ምክያቶች መሆኑን መንግሥት በቅንነት እንዲረዳ፤

6 የህዝባቸውን ህጋዊ ጥያቄና ፍትሓዊ ትግል የደገፉ የብሔሩ ተወላጅ ምሁራንንና የመንግሥት ሰራተኞችን ከኃላፍነታቸው ማንሣት፣ ማሸማቀቅ፣ እንደዚሁም በንግዱ ማህበረሰብና በወጣቶች ላይ የሚፈጸም ወከባ፣ ጫናና ማስፈራራት በአስቸከይ እንዲቆም፤

7 የወላይታ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑ ታውቆ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋበማስመሰል በሕዝቡ ታሪክ ላይ ጥላሸት በመቀባት የሥነ ልቦና ጥቃት ለማድረስ የሚሞክሩ ኃይሎች ሁሉ ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ፤

8 የፌደሬሽን ም/ቤትም የኢትዮጵያ ብሔሮችና ህዝቦችን ያለ አድሎ በእኩል በማዬት በሕገ-መንግስቱ መስፈርት መሠረት ባጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ምርጫ ቦርድ ህዝበ-ውሳኔ እንዲዘጋጅ እንዲያደርግ፤

9 በመጨረሻም መንግሥት ከሠፊው የወላይታ ህዝብ ጋር ሰላም እንዲፈጥር፣ ለዚሁም የሐገር ሽማግሌዎችን፣ የሀይማኖት መሪዎችን፤ የብሔሩ ታዋቂ ግለሰቦችንና ምሁራንን በጋራ በማወያየት መንግሥትና ህዝብ በመካከላቸው መተማመንን፤ በአከባቢው ዘላቂ ሠላምንና መረጋጋትን እንዲፈጥር በአጽንኦት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!

በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር (AWANA)

One Comment on “በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማኅበር በወላይታ ህዝብ ላይ በክልል መዋቅር ጥያቄ ምክያት እየደረሰ ስላለው ሕገ-መንግሥታዊና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ October 17, 2020

  1. wow! Endih ke Gonachin sitkomu ender yamribinal meselachihu Jegnoch hulem be libachin nachihu… digafachihu ayileyen

Leave a reply to Wondimu Samuel Herano Cancel reply